ዓላማዎችና የጊዜ ዝርዝር
ይህ ዘርፈ ብዙ የጥናት መስክ በተለይም የአርኪኦሎጂ ፕሮጀክት በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ የላሊበላን አካባቢ (ላስታን) ስለ ተቆጣጠሩት የአማራ ህዝቦች ያለንን እውቀት የበለጠ ለማሳደግ ይፈልጋል፡፡
እኛ የአካባቢውን ማህበረሰብ ባህሉን ለመረዳትና ለማወቅ ፍላጎት አለን፡፡ ፕሮጀክቱ ስነ-ህይወታዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊና ቁሳዊ ትርጉምን በማብራራት በአገው ቋንቋ ተናጋሪዎችና ወደ አካባቢው በመጡት የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች መካከል የተደረጉትን የግንኙነት ውጤቶች የማብራራት አላማ አለው፡፡
ለዚህም ቁልፍ መለኪያዎችን በመመልከት ጥናት በምናደርግባቸው መዳረሻዎች (sites) የንጽጽር መረጃ ቋትን እየገነባን ነው፡፡ እነዚህም የመልክዓ-ምድር አጠቃቀም፣ ስነ-ህንጻ፣ የሸክላና ባህላዊ ቁሶች፣ የብረት ውጤቶች፣ የግድግዳ ስዕሎችና ሌሎች ልዩ ልዩ አይነት ገጽታዎች ያላቸው እንደ ዋሻ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ግድግዳዎችን ያስጌጡ የዝቅተኛ እርከኖች ቅርጾች ተስተውለዋል፡፡ ጎን ለጎንም የሚስተዋሉት የመካከለኛው ዘመን የግድግዳ ላይ ስዕሎችም በግልጽ ከንጉስ ይኩኖ አምላክ ጋር የተዛመዱ ናቸው፡፡
በአካባቢው የተገኙ የመካከለኛው ዘመን ሸክላዎችን በአይነታቸው በመመደብ (typology) በሌሎች የኢትዮጵያ መዳረሻዎች ላይ ከተገኙ ሸክላዎች ጋር ለማነጻጸር አቅደናል፡፡ ከንጉስ ይኩኖ አምላክ ጋር ተያያዥነት ያላቸው በእያንዳንዱ መዳረሻዎች ላይ የተገኙ የሰው ቅሪቶች በዛጔ ስረወ-መንግስት ከተሰራው ይምርሓነ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ካሉት አጽሞችና ሳይፈርሱ ከቆዩ አስከሬኖች ጋር ይነጻጸራሉ፡፡
ምንም እንኳ እኛ በአካባቢው ስላለው የመካከለኛው ዘመን ላይ ትኩረት ያደረግን ቢሆንም ከዚያ በፊት ስለነበረው ታሪክ ካልተጠቀሰ ግልጽ ሊሆን አይችልም፡፡
ስለዚህ እኛ በዋናነት ለምንፈልገው ጥናት ሊረዳን ስለሚችል ሁሉን አቀፍ ዘዴ በመጠቀም ሁሉንም ታሪካዊና ቅድመ-ታሪክ መረጃዎችን እንመረምራለን፡፡ ሁሉም የስራ ደረጃዎችና ጊዚያት ከግምት ውስጥ ተወስደው በትክክል ተመዝግበው ይተረጎማሉ፡፡ ለራሳችን ተዛማጅ ቁሳቁሶችን ማቅረብ ብቻ ሳይሆን በተጨማሪም ለወደፊት ለሚመጡ የአርኪኦሎጂ ስራዎች መረጃ ለመስጠት ነው፡፡
2001 ዓ.ም (2009 G.C)
የፕሮጀክቱ የመጀመርያ የመስክ ጉዞ የመሬት ገጽታ ላይ ያሉ ቁሶችን መሰብሰብ እና በርካታ መዳረሻዎችን በጥንቃቄ መመዝገብን ያካተተ ነበር፡፡ ለፕሮጀክቱ ስኬት ድጋፍቸውን ለማግኘት አንድ ወሳኝ ክፍል ከአካባቢው ማህበረሰቦች ጋር ተሳትፎ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም ይህ ፕሮጀክት በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን እንዲሁም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ፓትሪያሪክ ፍቃድን አግኝቷል፡፡
2002 ዓ.ም (2010 G.C)
የፕሮጀክቱ ዳይሬክተር በጤና ችግር ምክንያት መጓዝ ስላልቻለች ሁለት ኢትዮጵያዊ የቡድኑ አባላት አቶ ሃብታሙ ተስፋዬ እና አቶ አበበ መንግስቱ በ2001 ዓ.ም ያልተጎበኙ የጥናቱ መዳረሻዎች ላይ ተጨማሪ የመጀመርያ ደረጃ ጥናቶችን አድርገዋል፡፡ ስለሆነም እነዚህ ጥናቶች የፕሮጀክቱን ወሰን ለመግለጽ ይረዳሉ፡፡
2010 Tania Tribe's report for SOAS on her seed-corn funded research
2004 ዓ.ም (2012 G.C)
ከሚያዚያ-ግንቦት 2004 ዓ.ም ድረስ በገነተ ማርያም ዘላቂና ጥልቅ የሆነ የአርኪዮሎጅ ጥናት ለዶክትሬት የምርምር ስራው በብራየን ክላርክ የተጀመረ ሲሆን ዓላማው የመካከለኛው ዘመን የንጉስ ድንኳን (royal campsite) በዚያ ሊኖር ይችል እንደነበረ ለማሳየት ነበር፡፡
2005 – 2006 ዓ.ም (2013 G.C)
ከመጋቢት-ሚያዝያ 2005 ዓ.ም የፕሮጀክቱ ቡድን አባላት የአጼ ይኩኖ አምላክን አያት ቦታና የእስር ቤቱን ተራራ ጨምሮ በገነተ ማርያምና በዋሻ ሚካኤል የዳሰሳ ጥናት ሥራ አካሂዷል፡፡ በዚህ ጊዜ ብራየን የመስክ ስራውን የቀጠለ ቢሆንም ነገር ግን በአፈር መሸርሸርና አንድ ስፍራ ላይ በሚደረግ የረጅም ጊዜ ምክንያት እርሻ ለጥናቱ አጋዥ የሆነውን የአለት ንብብር ማግኘት አልተቻለም፡፡ በዚህም የተነሳ ብርያን ጥናቱን ጥልቅ ወደሆነ አከባቢያዊ ትንተና ቀይሮታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ ከገነተ-ማርያም ቤተክርስቲያን ግቢ ውጭ የተወሰነ ቁጥጥር የነበረበት ቁፋሮ እንዲያከናውን ፍቃድ ተሰጥቶታል፡፡ ቦታው ላይም ለመዳረሻ መንገድ ተብሎ በተደረገ ቁፋሮ ቀደም ሲል ያልታወቀ የመቃብር ቦታ በከፊል ተቆርጦ ነበር፡፡ በጊዜ እጥረት ምክንያት ሶስት የሙከራ ጉድጓዶች ብቻ የተቆፈሩ ሲሆን የተገኙት አጽም እና ቁሳቁሶች ተመዝገበውና ተነስተው በላሊበላ ባህል ማእከል ተቀምጠዋል፡፡ በ2006 ዓ.ም ህዳር ወር የተገኘውን ቅሪተ አካል ለማጥናት በይምርሓነ ክርስቶስ ከተሰባሰቡት አጥንት ጋር አነጻጽሮ ለመመርመር በህዳር ወር ከአጥንት ተመራማሪዋ ኬይቲ ታከር ጋር ተመልሰናል፡፡
2007 ዓ.ም (2014-2015 G.C)
በዚህ አመት በህዳር ወር ላይ ከገነተ ማርያም ግቢ ውጭ የተደረገው ስልታዊ ጥናት በ2005 ዓ.ም የተገኙትን ቀብሮች መጠን/ሁኔታ ያብራራ ነበር፡፡ በተጨማሪም አንድ ክፍት የሆነ የተቆረጠ አለትን ጨምሮ በርካታ መቃብሮች ሙሉ በሙሉ ተቆፍረዋል፡፡ በዋሻ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ከንክኪ ነጻ የሆነ ስራ የተደረገ ሲሆን ከማህበረሰቡ ጋር ውይይታችንን ቀጥለናል፡፡
2014 Fieldwork report for the Society of Antiquaries of London
-
በላሊበላ የባህል ማዕከል ውስጥ በተሰበሰቡ የፕሮጀከቱ ቁሳቁሶች ላይ ማለትም የሰው ቅሪቶች፣ የሸክላ ናሙናዎችና ሌሎች ትንንሽ ግኝቶች ላይ የምርምር ስራ ለመስራት የቡድኑ አባላት ወደ ላሊበላ ጉዞ አድርገዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የጉዞው አላማ የተከፈቱ መቃብሮችን ለመሙላት ነበር፡፡
2009 ዓ.ም (2017 G.C)
ቁፋሮው በሚያዝያ ወር በገነተ ማርያም እንደገና የተጀመረ ሲሆን ስራው የተጀመረው ካህናቱ እድሜ ጠገብ መቃብሮች ያሉት በውስጠኛው የቤተክርስቲያኑ ግቢ ውስጥ ይሆናል ብለው ባመኑበት ቦታ ነው፡፡ ግቢው ላይ ጥልቅ የሆነ የዳሰሳ ጥናት ተደርጓል፡፡ ላመል ያህል ቁፋሮ የተጀመረ ቢሆንም ከማህበረሰቡ አባላት ተቃውሞ በመነሳቱ የተቆፈሩትን ጉድጓዶች እንደገና እንድንሞላና ያቀድነውን ስራ ወደ ሌላ ጊዜ እንድናስተላልፍ ተገደናል፡፡
2012 ዓ.ም (2019-2020 G.C)
በዚህ ጊዜ የተደራሽነት (Outreach) ስራ የተሰራ ሲሆን በፕሮጀክቱ የገንዘብ ድጋፍ ሰጭነት ከግዕዝ ወደ አማርኛ ቋንቋ ተተርጉሞ በመጨረሻ ላይ የታተመው የንጉስ ይኩኖ አምላክን ታሪክ የያዘው ገድል የመጀመርያው የህትመት ስራ ለገነተ ማርያም ቤተክርስቲያን ማህበረሰብ ለምዕመናን እና ለጎብኝዎች ለሽያጭ የሚያቀርቡት 1000 ቅጅዎች ተበርክተዋል፡፡
-
ካለፉት ሁለት አመታት በላይ በተደረገ ረዥም ድርድር በኋላ ቡድኑ በግንቦት ወር ውስጥ የሚቀጥለውን የፕሮጀክቱን ደረጃ ለማቀድ በጥር ወር ወደ ገነተ ማርያም እንደገና መጥቶ ነበር፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ የኮሮና (COVID-19) ወረርሽኝ በዚህ አመት ተጨማሪ የመስክ ስራ እንዳይሰራ ከልክሏል፡፡ ለመስራት ምቹ በሚሆንበት ጊዜ ወዲያውኑ ስራችንን ለመጀመር እቅድ ያለን ሲሆን እሱም በ2013 ዓ.ም እንደሚሆን ተስፋ አለን፡፡