top of page

ታሪካዊ ዳራ

ዘመናዊቷ ኢትዮጵያ  በአፍሪካ ቀንድ ሰፊ ክፍል የያዘች ስትሆን ከ3-6 ሚሊዮን አመት ያስቆጠሩ በርካታ የሰው ልጅ ቅሪተ አካላት መገኛ ነች፡፡ እነዚህም “ኢትዮጵያን የሰው ልጅ መገኛ” የሚል ማእረግ ያስገኙላትና በኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ከተገኙት መካከል አርዲፒቲከስ ራሚደስ (አርዲ) እና አውስትራሎፒቲከስ አፋረንሲስ (ሉሲ በኢትዮጵያ ደግሞ ድንቅነሽ) ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም ዘመናዊው የሰው ልጅ (Homo sapiens) በአካባቢው ከ200, 000 አመት በላይ ኖሯል፡፡


በቀጠናው ያለው የታሪክ ጊዜ የሚጀምረው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ3000 አመት ገደማ ጥንታዊ ግብፆች ከፑንት ጋር ያደርጉት የነበረውን የንግድ ግንኙነት በማጣቀስ ነው፡፡ ከተወሰኑ 2000 አመታት በኋላ በሰሜን ኢትዮጵያና በኤርትራ D’MT ምንአልባትም ዳ’አማት (Da’amat) ተብሎ የሚጠራው ግዛት ተነስቷል፡፡ ይህ ግዛት በተወሰነ መጠን ከቀይ ባህር ማዶ አሁን የመን በሚባለው አገርም በተወሰነ ደረጃ ተጽዕኖ ነበረው፡፡  

የደአማት መንግስት መነሻውን ከክርስቶስ ልደት በፊት የመጨረሻዎቹ ዘመናት ባደረገው የአክሱም ስርወ-መንግስት የተተካ ሲሆን ይህ ስርወ-መንግስትም ከክርስቶስ ልደት በኋላ በመጀመርያው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ጉልህ የሆነ ክልላዊ ኃይል እየሆነ መጥቷል፡፡ ለብዙ መቶ አመታት አክሱም በባዛንታይን ግዛትና በህንድ መካከል በቀይ ባህር ለነበራቸው ንግድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ የዚህ ስርወ-መንግስት ተከታታይ ገዢዎችም ግዛታቸውን በሰሜን ወደ ሱዳን፣ በምስራቅ ወደ የመንና በደቡብ ባመዛኙ በአሁኑ ጊዜ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ወደሚባለው ክፍል አሳትመዋል፡፡ በዚህም ወቅት የራሳቸውን ሳንቲም አሳትማዋል፡፡ በአክሱም ከተማ እስከ አሁን ድረስ  ቆሞ በሚታየው ሀውልት የሚንጸባረቅ ልዩ የአሰራር ዘዴ ያለውን የኪነ-ህንጻ ጥበብ አሳድገዋል፡፡ የሴሜትክ ቋንቋ የሆነው ግዕዝ የመንግስት ቋንቋ  በመሆን አገልግሏል፡፡ ንጉስ ኢዛና በ330ዎቹ ዓ.ም አካባቢ የክርስትና ሃይማኖትን 

ከተቀበለ በኋላ አዲሱ ኃይማኖት ቀስ በቀስ ወደ ህዝቡ ተሰራጭቷል፡፡ በ7ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የእስልምና ሃይማኖት ከመጣ በኋላ የቀይ ባህር ንግድ በእስላሞች እጅ ሲወድቅ የአክሱም ስርወ-መንግስት ተንኮታኩቷል፡፡ በተጨማሪም የዚህን ስርወ-መንግስት የመጨረሻዎቹን አመታት እውነት የሚያረጋግጡ ጥቂት መዛግብት አሉ፡፡

ከዚያም የስልጣን ማዕከሉ ከአክሱም የአየር ላይ ልኬት 230 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ወደሚገኘው የአገው ቋንቋ ተናጋሪ ህዝቦች ይኖሩበት ወደ ነበረው ደቡብ አቅጣጫ የላስታ ደጋማ አካባቢ ተዛውሯል፡፡ በዚህ አካባቢ የዛጔ ስርወ-መንግስት ከ10ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ጀምሮ እስከ 1262 ዓ.ም ድረስ ለ300 አመታት ያህል ገዝቷል፡፡ 


እነሱም (የዛጔ ስረወ-መንግስት ነገስታት) ብዙዎቹን የአክሱምን ስልጣኔ እንደያዙ አስቀጥለዋል፡፡ በተለይም የክርስትና እምነትን፣ ግዕዝ ቋንቋን ለአስተዳደር መግባቢያነት መጠቀም፣ ፈርጀ ብዙ የኪነ-ህንጻ አሰራር ዘዴዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ከዚህ ስርወ-መንግስት ቀደምት ነገስታት አንዱ የነበረውና ከዛጔ ስርወ-መንግስት ዋና ከተማ ሮሓ በስተሰሜን በኩል የግማሽ ቀን የእግር ጉዞ ላይ በስሙ በሚጠራው ቤተክርስቲያን ውስጥ የተቀበረው ቅዱስና ንጉስ ይምርሓነ ክርስቶስ አንዱ ነበር፡፡

በኋላ ላይ የስርወ-መንግስቱ ዋና ከተማ ከ12-13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነገሰውና የሰማያዊቷን እየሩሳሌምን በማስመሰል ከጠንካራ አለት ትልቅ የቤተክርስቲያን ስብስቦችን በማነጽ በማህበረሰቡ ዘንድ በተመሰገነው ንጉስና ቅዱስ ላሊበላ ስም እንደገና ተሰየመች፡፡ 

ሆኖም አሁን ላይ አርኪኦሎጅስቶች እንደሚጠቁሙት እነዚህ አብያተ ክርስትያናት ከ10ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በሂደት የተፈለፈሉ መሆናቸውን ነው፡፡ በመጨረሻም በስልጣን ሽኩቻ በተነሳ ግጭት የዛጔ ስርወ-መንግስት ተጋላጭ ሆነ፡፡ በ1262ዓ.ም ከዛጔ ስርወ-መንግስት ግዛት ደቡባዊ ዳርቻ የመጣው የአንድ አለቃ የልጅ ልጅ የሆነው ይኩኖ አምላክ የመጨረሻውን የዛጔ ገዥ የነበረው ይትባረክን ድል እንዳደረገው ይታመናል፡፡ ከዚያም የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነውን የሰሎሞን ስረወ-መንግስትን መስርቷል፡፡ ይህ ስርወ-መንግስት የመጨረሻው የኢትዮጵያ ንጉስ  አጼ ኃ/ስላሴ እስከወደቀበት 1966 ዓ.ም ድረስ ቆይቷል፡፡ ስርወ-መንግስቱ የዘር ሃረጉን ከአክሱም ስርወ-መንግስት የመጨረሻው ንጉስ ከነበረው ድልናኦድና በእርሱ በኩል ከንግሰተ ሳባና በመጽሀፍ ቅዱስ ከተጠቀሰው ንጉስ ሰሎሞን ከተወለደው ቀዳማዊ ሚኒልክ ቀጥተኛ የዘር ሀረግ አለኝ በማለት ከእሱ በፊት የነበረውን ስርወ-መንግስት ከስልጣን በሃይል መንጠቁ በቂ ምከንያት ነው (ህጋዊ ነው) ብሎ ያምናል፡፡ በሌላ በኩል የዛጔ ገዢዎች ሰለሞናዊ ያልነበሩና ያለአግባብ ዙፋን የያዙ ናቸው ብሎ ይከሳል፡፡

Däbrä Sina Gorgora 2.jpg

ቀደም ያሉት የሰለሞን ስርወ-መንግስት ነገስታት ቋሚ ዋና ከተማ አልነበራቸውም፡፡ ነገር ግን እየተንቀሳቀሱ የሚመሩበት የንጉስ ድንኳን ነበራቸው፡፡ ይኩኖ አምላክና ከእሱ በኋላ የመጡት ንጉሶች በዋናነት ንጉስ ዐምደ ጽዮን (14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን) እና ዘርዓ ያዕቆብ (15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን) ግዛታቸውን ለማጠናከር በሰሜን ኢትዮጵያ ደጋማ ቦታዎች ላይ በተደጋጋሚ ወታደራዊ ዘመቻ አድርገዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም በደቡብ ምስራቅ፣ በደቡብና በምዕራብ አካባቢ የነበሩ ጎረቤቶችን በመውረር የእስልምና ወይም የአካባቢ እምነት ተከታዮችን ወደ ክርስተና እምነት ለውጠዋቸዋል፡፡ 

በተጨማሪም መልዕክተኞቻቸውን ወደ ሮም፣ ወደ ፖርቱጋልና ሌላ ቦታ ይልኩ ነበር፡፡ በዚህም በሱልጣን ኢማም አህመድ ቢን ኢብራሄም አልጋዚ የተመራው የአዳል ጦር 1533-1535 ዓ.ም የክርስቲያን ነገስታት ላይ ያደረገውን ወረራ ለማገዝ ፖርቱጋል ወታደሮቿን ልካለች፡፡ በ1625 ዓ.ም በንጉስ ፋሲለደስ እሲኪባረሩ ድረስ የእየሱስ መልእክተኞች (እየሱሳዊያን) በአገሪቱ ቆይተዋል፡፡ በተጨማሪም ፋሲለደስ ጎንደርን የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አድርጓል፡፡ በጎንደር ዘመን መንግስት መረጋጋት የተረጋገጠበት ሲሆን የምርምር ህይወትና ስነ-ጥበብም ያደገበት ዘመን ነበር፡፡ ይሁን እንጅ በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ በመሬት ከበርቴዎች (Land Lords) እና በሃይማኖተኛ ቡድኖች መካከል የመረረ ግጭት አገሪቱን ለ100 አመታት ያህል በቀውስ እንድትጥለቀለቅ አድርጓታል፡፡ በ1847 ዓ.ም በንጉስ ዳግማዊ ቴዎድሮስ ስልጣን መውጣት አገሪቱ ወደ ዘመናዊነት ደረጃ ብትወጣም ከብሪታንያ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት የብሪትሽ መንግስት እሱን ለመቅጣት ወታደር በመላክ በ1860 ዓ.ም መቅደላ ላይ በተደረገበት ከበባ ቴዎድሮስ ራሱን አጥፍቷል፡፡ ብዙም ሳይቆይ አጼ ዳግማዊ ሚኒልክ ጣልያን አገሪቱን  ለመቆጣጠር የነበራትን እቅድ በ1888 ዓ.ም አድዋ ላይ ሰራዊቷን ድል በማድረግ ገትቷል፡፡ ከዚያም የሶማሊያ፣ የኦሮሞና ሌሎች ህዝቦች ይኖርባቸው የነበሩትን የደቡብና የምስራቅ ዝቅተኛ ቦታዎችን በማዋሃድ የኢትዮጵያን ግዛት አሁን ላይ እሰካለው ወሰን ድረስ አስፋፍቷል፡፡

ከ1922-1966 ዓ.ም ኢትዮጵያን የገዛው የመጨረሻው ንጉስ አጼ ኃይለ ስላሴ ምንም እንኳ ከ1928-1933 ዓ.ም በተካሄደው የጣልያን ወረራ ወቅት ወደ ውጭ ለመሰደድ ቢገደድም ዘመናዊነትን በኢትዮጵያ አስቀጥሏል፡፡ 


ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አጼ ኃይለ ስላሴ ኤርትራን እንደገና ወደ ኢትዮጵያ መቀላቀሉ ኤርትራውያኖችን ወደ ነጻነት ትግል እንዲያመሩ አድርጓል፡፡ በ1966 ዓ.ም የህበረተሰባዊ ደርግ የኃይለ ስላሴን ስርአት በማስወግድ በአብዛኛው ህዝብ የአኗኗር ዘይቤና ሃይማኖት ላይ ከፍተኛ የሆነ ተጽዕኖ ያደረሰውን ወታደራዊና አምባገነን መንግስት በህዝቡ ላይ ሲጭን የኤርትራውያኖች የነጻነት ትግል በመደበኛነት ተሳክቷል፡፡ በ1970ዎቹ የተከሰተው ርሀብ ህዝቡ ለተቃዋሚ ቡድኖች ድጋፉን እንዲጨምር ያደረገ ሲሆን በመጨረሻም በ1983 ዓ.ም አገዛዙ ከስልጣን ተወግዷል፡፡ 


በአቶ መለስ ዜናዊ የተመራው አዲሱ ህገ-መንግሳታዊ መንግስት ከምዕራባዊያን ሃይሎች ጋር ግንኙነቱን እንደገና በማስተካከል የተቃዋሚ ቡድኖችን በጥብቅ መቆጣጠር ችሏል፡፡ ሆኖም ይህ መንግስት በግልጽ ለትግራዮች ባለው ወገንተኝነት ምክንያት በሌሎች ቡድኖች ዘንድ ቅሬታና መከፋትን ፈጥሯል፡፡ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስተር ዐብይ አሕመድ ሚዛኑን ለማስተካከል ያደረጉት ጥረት ተስፋ ተጥሎባቸው የነበሩ ስኬቶችን ገና አላሟላም፡፡ አሁንም አልፎ አልፎ ብጥብጥ ይከሰታል፡፡

bottom of page