top of page

ፕሮጅከቱ

ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ የሰለሞናዊና የዛጔ ነገስታት ግንኙነት ፕሮጀክት የጥናት ቡድን  የሰሜን ኢትዮጵያን ከፍተኛ ቦታዎች የመካከለኛው ዘመን ታሪክን እየመረመረ ይገኛል፡፡ በተለይም የአማርኛ ቋንቋ ተነጋሪው ንጉስ ይኩኖ አምላክ በስልጣን ላይ የነበረውን የአገው ቋንቋ ተናጋሪ የዛጔ  (የላስታ) ስርወ-መንግስትን በ13ኛው መቶ ክፍል ዘመን መገባደጃ ላይ ስልጣን የነጠቀበትንና የሰለሞን ስርወ-መንግስት ተብሎ የሚታወቀውን የመሰረተበትን ቁሳዊ ሁኔታዎች ለመረዳት እንሞክራለን፡፡ 


ከላሊበላ ቀጥታ የአየር ላይ ልኬት 11 ኪ.ሜ ደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ ላይ በሚገኘው የገነተ ማርያም ቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉት የግድግዳ ላይ ስዕሎች ቀደም ሲል ለጋሽ የነበረውን የታዋቂውን የኢትዮጵያ ንጉስ ይኩኖ አምላክ አስደናቂ ወካይ ምስል የሚያካትቱ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ተመሳሳይ የአሳሳል ዘይቤ ያላቸው ስዕሎች በአካባቢው በሚገኙ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ሲሆን ነገር ግን  የዛጔ ስርወ-መንግስት የስልጣን ማዕከል በነበረው የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ አይገኙም፡፡ ይህ ተቃርኖ የውቅርና የዋሻ ውስጥ አብያተ ክርስትያናት አንዱ ከሌላኛው ጋር ያላቸውን ተዛምዶ በማነጻጸር በሁለቱ ስርወ-መንግስታት መካከል ያለውን የአርኪኦሎጂ አሻራ ግንኙነት እንድንፈልግ አነሳስቶናል፡፡ 


ፕሮጀክቱ የተለያዩ ገጽታ ያላችውን በመሬት ውስጥ የተቀበሩ የታሪክ ቅርሶች የጥናት መስኮችን የሚያካትት ሲሆን ከነዚህም ውስጥ የመስክ አርኪኦሎጂ ጥናት (የሰውን ቁሳዊ ባህል በመተንተን የዳሰሳ ጥናትና ቁፋሮን በመጠቀም ይተገብራል)፣ የስነ-መልክዓ ምድር አርኪኦሎጂ (ሰዎች ቀደም ባሉት ጊዜያት በእነሱ ዙሪያ ያለውን አካባቢ በምን አይነት መንገድ ገንብተው ተጠቀሙት የሚለውን የሚያጠና ዘርፍ ነው)፣ የስነ-ህይወት አርኪኦሎጂ (የሰውን፣ የእንስሳትን እና የእጽዋትን ቅሪት አካል የሚያጠና የትምህርት ዘርፍ)፣ የሸክላ ጥናቶች፣  ሥነ-ጥበባዊ ታሪክና ቅርስና እንክብካቤን የሚያጠቃልል ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር በፕሮጀክታችን ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን በማቅረብ ለማህበረሰቡ ተጨማሪ እሴት ለማምጣትም እየሞከርን እንገኛለን፡፡      

bottom of page