top of page

ይምርሓነ ክርስቶስ

ይህ መዳረሻ (የይምርሓነ ክርስቶስ የዋሻ ውስጥ ቤተክርስትያን) በዛጔ ስርወ-መንግስት በቅዱስ ንጉስ ይምርሓነ ክርስቶስ የተሰራ ሲሆን ከላሊበላ ከተማ ሰሜን አቅጣጫ የአየር ላይ ልኬት 12 ኪ.ሜ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ 


በሰሜናዊ አቅጣጫ የሚገኘውን ተራራማ ቦታ በማቋረጥ የግማሽ ቀን የእግር ጉዞ በመጓዝ ወይም ዙርያ ጥምጥም የሆነውን የመኪና መንገድ በመጠቀም በተሸከርካሪ በሰዓታት ውስጥ ቦታው ላይ በመድረስ 15 ደቂቃዎችን የሚወስደውን በደረጃ የተሰራውን ቀጥ ያለ ያቀበት መንገድ ከወጡ በኋላ የዋሻ ቤተክረስቲያኑ ውስጥ ይደረሳል፡፡ መዳረሻው ያለበት ቦታ ከባህር ጠለል በላይ 2700 ሜትር ወደ አቡነ ዮሴፍ ተራራ በሚያመራው ጥቅጥቅ ደን ከተሸፈነ ቦታ ላይ ሲሆን በውስጡ ሁለት የህንጻ መዋቅሮች ማለትም ቤተክርስቲያኑና ’ቤተ-መንግስቱ’ ወይም ’ግምጃ ቤቱ’ በተጨማሪም የንጉሱ መቃብርና ሁለት ትንንሽ ቀብሮች እንዲሁም የመነኩሳትና የተጓዦች ናቸው ተብሎ የሚታመንባቸው የአጥንት ስብስቦችና ሳይፈርሱ የቆዩ አስከሬኖችን ያሉበትን 50 ሜትር ስፋት ያለውን ትልቅ ዋሻ የያዘ ነው፡፡


ቤተክርስትያኑ በተለዋዋጭ የድንጋይና ጥቁር እንጨት ንብብር መስመሮች መፈጠር ምክንያት ከአክሱማውያን ስርወ-መንግስት በኋላ የመጡትን ኪነ-ህንጻዎች የንብብር-ኬክ አይነት ገጽታ አለው፡፡ ይህ ቤተ ክርስቲያን መቅደሱ በጉልላትና ቅድስቱ ደግሞ ኩርቻ ቅርጽ ባለው ጣራ ተሸፍኗል፡፡ 


በዶ/ር መንግስቱ ጎበዜ የተደረገው የራዲዮ ካርቦን ጥናት ቤተክርስቲያኑና ቤተመንግስቱ የተሰራበት ጊዜ ከ11-12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ የቤተክርስቲያኑ የውስጠኛ ክፍል በዚህ ፕሮጀክት ከተጠኑት/ከተመረመሩት ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት የተለዩ በሆኑ ስዕሎች ተሸፍኗል፡፡

 

bottom of page